በኦፊሴላዊ ስሟ የምናውቃት ሲሼልስ ሪፖብሊክ 115 ደሴቶችን ሰብስባ የያዘችና በሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ ተንሳፍፋ የምትገኝ ጢንጥዬ ደሴትማ አገር ናት፡፡ ከሁሉም ደሴቶች በትልቅነቱ የሚታወቀው ከተማ ቪክቶሪያ ይሰኛል፡፡ ቪክቶሪያ የሲሼልስ ዋና ከተማ ነው፡፡ ይህ ከተማ ከአፍሪካ ከፍለ-አህጉር ምስራቃዊ ግርጌ 1,500 ኪሎሜትሮችን ያህል ርቆ ይገኛል፡፡ በአካባቢው በቅርበት የሚገኙት ደሴቶቸና ግዛቶች ኮሞሮስን፣ ማደጋስካርንና፣ ሞሪሺየስን የፈረንሳይን የቅኝ ግዛቶች የሆኑትን ማዮቴንና ሪዩኒየንን በደቡብ፣ እንዲሁም ሞሊዴቪስንና በእንግሊዞች በቅኝ ግዛትነት የሚተዳደሩትን የቻጎስ ስብስብ ደሴቶች በምስራቅ በኩል ያካትታል፡፡ ሲሼልስ ባለፈው የ2020 የአውሮፓውያን የዘመን ቀመር ግምት መሰረት 99,258 የሆነ አነስተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ያላት አፍሪካዊት ሚጢጢዬ ደሴትማ አገር ናት፡፡
በ16ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን በአውሮፓውያን እስከተገኘች ድረስ፣ ሲሼልስ ምንም ሰው የማይኖርባት ጭው ያለች ሰው-አልባ ደሴት ነበረች፡፡ በብሪታኒያ ቁጥጥር ስር እስከሆነች እስከ 18ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በፈረንሳይና በብሪታኒያ በይገባኛል ክርክር ውስጥ ቆይታለች፡፡ ሲሼልስ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1976 ከብሪታኒያ የቅኝ አገዛዝ ነፃ እንደወጣች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከ21ኛው ክፍለ-ዘመን መነሻ አንስቶ ሲሼልስ ከሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች በተሻለ የነፍስ ወከፍ ገቢ ደረጃ ላይ ትገኝ ነበር፡፡ በዓለም ባንክ መስፈርት መሰረት፣ ሲሼልስ ከፍተኛ ገቢ ያላት በቸኛ አፍሪካዊት አገር በሚል የደረጃ ሰንጠረዥ የያዘች ደሴት ናት፡፡ ይህች ድነቅ ደሴት ከአለማችን ካሉ ሀገራት በቱሪዝም መስብህነቷ የተጨበጨበላት ናት፡፡
እንግዲህ ይህችን ወደመሰለች አገር ነው ብሬክስሩ ትሬዲንግ አ.ማ. በዘንድሮው የበጀት ዓመት በስራ ትጋታቸው የአሸናፊነት በልጫን የተጎናፀፉትን ገፅታ ገንቢዎች የጉብኝት ጉዞ እንዲያደረጉ የወሰነው፡፡
የሲሼልስ አስደማሚ እውነታዎች
1. የወፍ ደሴት የሚባለው የሲሼልስ ክፍል ክብደታቸው እስከ 670 ፓውንድ (ውድ 304 ኪ.ግ ያህል) የሚደርስና ኤስሜራልዳ በሚል ስም የሚታወቁት የየብስ (የመሬት) ዔሊዎች መኖሪያ ነው፡፡
2. ኮኮ ደ’መር በሚል ስሙ የሚታወቀው ደሴት በዓለማችን በትልቅነቱ አቻ የለውም የሚባለውን የእህል ዘር (ሲድ) ያመርታል፡፡ በዕይታው የለውዝ መሳይ ምስልና ቅርፅ ያለው ዘር እስከ 33 ፓውንድ (15 ኪ.ግ) ይመዝናል ተብሎለታል፡፡
3. የሲሼልስ ዋና ከተማ የሆነው ቪክቶሪያ በዓለማችን በትንሽነቱ የሚታወቅ ዋና ከተማ ነው፡፡ ከአንድ ቀን ባነሰ ጊዜ ውስጥ የከተማውን ዙሪያ ከጥግ እስከ ጥግ በእግር ብቻ መዞርና ማሰስ እንደሚቻል መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
4. የጀምስ ቦንድ ደራሲ የሆነው ኢያን ፈሌሚንግ For Your Eyes Only በሚል ርዕስ ለተፃፉ የታሪክ ስብስቦቹ ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያግዘውን ተመስጦ ለማግኘትና በህይወቱ አንድ ጀብድ ለመስራት በሚል እ.አ.አ. በ1958 ሲሼልስን ጎብኝቷታል፡፡
5. የአዕዋፋት ፍሬ የሚባለው የደሴቲቱ ፍሬ በዚያች ትንሽ አገር፣ በሲሼልስ፣ በዝነኛነቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ፍሬ በጥብስ ሆነ በቅቅል መልክ ለምግብነት ይውላል፡፡ በዚህች ደሴት ላይ ተገኝቶ ይሄንን ፍሬ የተመገበ ሰው አንድ ቀን እንደገና ተመልሶ ወደ ደሴቲቱ ይመጣል የሚል ንግርት እንዳለ የነገራል፡፡